ፓርላማ የገቡ የቅንጅት አባላት የአመራሮቻቸው የዋስ መብት እንዲጠበቅ እንደሚታገሉ ገለፁ

ፓርላማ የገቡ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አባላት የታሰሩ የፓርቲው አመራር አባላትን የዋስ መብት ለማስጠበቅ እንደሚታገሉ ገለፁ። አባላቱ ከአፈ ጉባኤው ጋር የሚገናኙ ተጠሪዎቻቸውን ሰኞ እለት ባደረጉት ስብሰባ መርጠዋል።

የአባላቱ ተወካዮች አቶ ተመስገን ዘውዴ፣ አቶ አባይ አበበ፣ አቶ እንዳልካቸው ሞላ እና አቶ ሳምሶን ወ/ዮሐንስ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የቅንጅቱ አመራሮች በህገ መንግስቱ መሰረት የዋስትና መብታቸውን እንዲጠበቅላቸው እንደሚታገሉ ገልፀዋል።

ይህንንም ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው የመንግስት ክፍል እንደሚያቀርቡ የገለፁት አባላቱ የድርጅቱን ህልውና ለመታደግ ህገመንግስቱና የአገሪቱ ሕጎች በሚፈቅዱት መሰረት እንደሚንቀሳቀሱ አስረድተዋል።

የቅንጅቱ አመራሮች ፓርላማ እንደማይገቡ ከዚህ ቀደም የገለጹ መሆናቸውን በመጥቀስ እናንተ ከድርጅታችሁ ውሳኔ ውጭ እንዴት ፓርላማ ልትገቡ ቻላችሁ በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ «ቅንጅት አንድም ቀን ፓርላማ አልገባም ብሎ አያውቅም» በማለት አስተባብለዋል።

«ቅንጅት እንደ ድርጅት አሁንም አለ ለማለት ይቻላል?» በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠ/ሚ/ር መለስም ሆነ ሌሎች የኢሕአዴግ ፓርቲ አባላት የመሰላቸውን መግለጫ ሊሰጡ ይችላሉ። ነገር ግን የአንድን ድርጅት ሕጋዊነት የሚገልፀው የህግ ስርዓቱ ነው ብለዋል።

የፓርላማ አባላቱ አያይዘውም ወደ ፓርላማው የገባነውም እንደ ቅንጅት ተመዝግበን ነው። በቀጣይም የድርጅቱን ፕሮግራም እናስፈፅማለን። ከቅንጅቱ ጋር ምንም ዓይነት ልዩነት የለንም» ብለዋል።

ከሪፖርተር ታኅሣሥ 12 ቀን 1998

ሰለ እዚህ ዜና ዋርካ ስር በአማርኛ ይወያዩ !